በአፍሪካ የፊልም አዋርድ ላይ የታየው ከ500 ዳቦዎች የተሰራው ቀሚስ

የፎቶው ባለመብት, BBC/GIFT UFUOMA
ግንቦት 2 2018 ዓ.ም. ምሽት በናይጀሪያ ሌጎስ የተካሄደው 12ኛው የአፍሪካ ማጂክ የተመልካቾች ምርጫ ሽልማት የአፍሪካ ግዙፉ የፊልም እና የፋሽን ምሽት በመባል ይታወቃል።
የአፍሪካ ማጂክ ተመልካቾች ምርጫ ሽልማት (Africa Magic Viewers' Choice Award- AMVCA) የናይጀሪያ ዝነኞችን ጨምሮ ከደቡብ፣ ምዕራብና ምሥራቅ አፍሪካ አገራት የተወከሉ ስመ ጥር ተዋናዮች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት በድምቀት ተከናውኗል።
ኤኤምቪሲኤ በአፍሪካ የፊቸር ፊልም፣ የቴሌቪዥን ድራማ እና ዶክመንተሪ ስራዎች የላቀ ጥራት ያላቸው ይዘቶችና የጎላ ስራ ከውነዋል ተብለው በተመልካቾችና በከፍተኛ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተመረጡ ባለሙያዎች የሚሸለሙበት የሽልማት ስነ ስርዓት ነው።
እሁድ ግንቦት 2 2018 ዓ.ም. በናይጄሪያ በተካሄደው 12ኛው የአፍሪካ ፊልሞች አዋርድ ላይ ታዋቂ ሰዎች፣ የፊልም ባለሙያዎች እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በተለያዩ አልባሳት ተውበው ተገኝተዋል።
ከግዙፉ የአፍሪካ የመዝናኛ ይዘቶች አቅራቢው መልቲቾይስ አፍሪካ አማካኝነት በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው በዚህ የፊልም አዋርድ ዝግጅት ላይ የተገኙ ታዋቂ ሰዎች የአህጉሪቱን ባሕል ከማሳየት በዘለለ በአልባሳቶቻቸው ተፎካክረዋል።
በሌጎስ በሚገኘው ኤኮ ሆቴል በተካሄደው ዓመታዊ የአፍሪካ ፊልም፣ ቴሌቪዝን እና ዲጂታል ሥነ ጥበባዊ ስራዎች ሽልማት ምሽቱን ልዩ ውበት ያጎናጸፉት በርካታ አልባሳት መነጋገሪያ ነበሩ።
በዕለቱ ከተገኙት ስመ ጥር ሰዎች ሁሉ ግን የአንዷ ታዋቂ የቴሌቪዥን ተዋናይ አልባሳት የበለጠ መነጋገሪያ ሆና አምሽታለች።
የእውናዊ ቴሌቪዥን ዝግጅት ላይ በመሳተፍ ታዋቂነትን ያገኘችው እና ራሷን ኩዊን ሜርሲ አታንግ በማለት የምትጠራው ታዋቂ ተዋናይት ከ500 ዳቦዎች የተሰራ ዘርፋፋ ቀሚስ ለብሳ ተገኝታለች።
ሁለት ሠራተኞች በግራ እና በቀኝ ያጀቧት ኩዊን ሜርሲ በርካታ ረዳቶች የለበሰችውን ቀሚስ በቀይ ምንጣፍ ላይ እንድታሳይ በማገዝ ረድተዋታል።
አታንግ በዳቦዎች የተሸመነው ቀሚሷን ለብሳ በነጻነት መንቀሳቀስ የተቸገረች ቢሆንም የዕለቱ መነጋገሪያ ሆና ግን አምሽታለች።
ከዳቦ የተሠራ ቀሚስ የለበሰችው የዳቦ መጋገሪያ ንግዷን ለማስተዋወቅ መሆኑን የገለጸችው አታገንግ፣ የፋሽን ስራው ገበያ ማፈላላግ እንጂ ድንጋጤን መፍጠር ዓላማው እንዳልሆነ አስታውቃለች፥
"ንግዴን ለማስተዋወቅ ከዚህ ከአዋርድ ምሽቱ የበለጠ አመቺ ጊዜ የለም" ስትልም ተናግራለች።
ቀሚሱን ዲዛይን ያደረገችው የቲያና ኢምፓየር ባለቤት ቶይን ላዋን ስትሆን በኢንሳታግራም ገጿ ላይ "ሁሉም የራሱን ንግድ ይልበስ" በሚል መሪ ቃል ንቅናቄ መጀመሯን ተናግራለች።
በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ወዲያውኑ መነጋገሪያ የሆነው አልባሳቱ የተወሰኑት ሲያደንቁት አንዳንዶች ደግሞ ተችተውታል።
"የራስን ንግድ ከፊት ማስቀደምን ያሳየ" ሲሉ ያሞካሹት እንዳሉ ሁሉ ምግብን ማባከን ነው በማለት ያብጠለጠሉተም አልጠፉም።

የፎቶው ባለመብት, BBC/GIFT UFUOMA

የፎቶው ባለመብት, BBC/MOBOLAJI OLATUNDE

የፎቶው ባለመብት, Reuters














