የአሜሪካ መከላከያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረጋቸው ሰነዶች የሌላ ዓለም ፍጡራን 'መኖራቸውን' ያሳያሉ?

የፎቶው ባለመብት, US Department of Defense
የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታገን፤ ከዚህ ቀደም ያልታዩ ምንነታቸው ካልታወቀ በራሪ አካላት (ዩፎ) ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ይፋ አድርጓል።
በምድር ላይ ዩፎዎችን እንዳዩ የተናገሩ ሰዎች ምስክርነት እና ጠፈርተኞች ጨረቃ ላይ የተመለከቱትም በሰነዶቹ ተካትቷል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰነዶቹ ይፋ እንዲሆኑ ባስተላለፉት ትዕዛዝ መሠረት ትናንት በይረ መረብ ላይ ተለቅቀዋል።
"ብዙ ሰው ማወቅ ስለሚፈልግ" ሰነዶቹ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆኑ መወሰናቸውን ትራምፕ ገልጸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት አሜሪካውያን ስለ ዩፎዎች የማወቅ ጉጉታቸው ጨምሯል።
በአውሮፓውያኑ 2022 የአሜሪካ ምክር ቤት ከ50 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ዩፎዎች ውይይይት አድርጓል።
የአሜሪካ መከላከያ ኃይል ስለ ጉዳዩ ግልጽ መረጃ ለማቅረብ ቃል ገብቶም ነበር። ትናንት በመከላከያ መስሪያ ቤቱ ድረ ገጽ ላይ 161 ሰነዶች ወጥተዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከወራት በፊት በሰጡት ቃለ ምልልስ "ባዕዳን ፍጡራን (aliens) አሉ፤ ነገር ግን አላየኋቸውም" ማለታቸው ይታወሳል።
ባዕዳን ፍጡራን ሊኖሩ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ የተናገሩት ኦባማ፤ ሆኖም ግን እሳቸው ፕሬዝዳንት ሳሉ እነዚህ ፍጡራን ስለመኖራቸው "ምንም ማስረጃ" አለማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የኦባማን ንግግር ተከትሎ ትራምፕ "ስለ ባዕድ ፍጡራን፣ ምንነታቸው ስላልታወቀ የሰማይ ላይ ክስተቶች እና ከምድር ውጭ ስላለ ሕይወት" የተሰበሰቡ መረጃዎችን ፔንታገን ይፋ እንዲያደርግ ወስነዋል።
ሰነዶቹ ለዓሥርት ዓመታት የተሰበሰቡ ወታደራዊ ጽሑፎችን ያካትታሉ። በአፖሎ የጨረቃ ጉዞ ወቅት የቀረቡ ሪፖርቶች እና ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ ፍጥረቶች (ዩፎዎች) አይተናል ያሉ ሰዎች ምስክርነትም ተካትቷል።
በተጨማሪም የአፖሎ 11፣ አፖሎ 12 እና አፖሎ 17 የጠፈር ተመራማሪዎች ሪፖርቶች ለሕዝብ ይፋ ተደርገዋል። በአውሮፓውያኑ ከ1960 እስከ 1970 ድረስ ጨረቃ ላይ የማረፍ ተልዕኮ አካል የነበሩ ጠፈርተኞች ያቀረቧቸው ሪፖርቶችንም ያካትታል።
የአፖሎ 11 ጠፈርተኛ በዝ አልድሪን በ1969 በሰጠው ቃለ መጠይቅ እንደተናገረው፤ በጨረቃ ጉዞ ወቅት ለማስረዳት የሚከብዱ ነገሮችን ተመልክቷል።
"አንዳች የብርሃን ምንጭ ተመልክቻለሁ። ምናልባት ጨረራ ሊሆን ይችላል ብለን ወስደነዋል" ብሏል።
በ1969 ጨረቃ ላይ የተራመደው እና የአፖሎ 12 አባል የነበረው ጠፈርተኛ አለን ቢን "የብርሃን ቅንጣቶች እና ጨረሮች" መመልከቱን ተናግሯል።
እነዚህ የብርሃን ፍንጥቅጣቂዎች "ከጨረቃ ያመለጡ" እንደሚመስሉ ገልጾ "ሕዋ ላይ ሲንሳፈፉ" ነበርም ብሏል።
በ1972 በአፖሎ 17 ተልዕኮ ውስጥ የነበሩ ሁለት ጠፈርተኞች መንኮራኮር ውስጥ ሳሉ የብርሃን ነጸብራቅ ማየታቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካ የነጻነት ቀን ሲከበር የሚለኮሱ ርችቶችን የሚመስል ብርሃን ማየቱን ጠፈርተኛው ጃክ ሽሚት ተናግሯል።
ብርሃኑ ከበረዶ አካል ላይ የተንጸባረቀ ሊሆንም እንደሚችል ገልጿል።
ፔንታገን ይፋ ካደረጋቸው ሰነዶች መካከል የድምጽ ቅጂ ይገኝበታል።
በ1965 በተደረገው ጄምኒ 7 የሕዋ አሰሳ ጠፈርተኛው ፍራንክ ቦማን ምድር ላይ ከሚገኙ ባልደረቦቹ ጋር ይነጋገራል።
"በትሪሊየኖች የሚቆጠሩ ጥቃቅን ቅንጣቶችን" በመንኮራኩሩ በስተግራ በኩል ማየቱን ለናሳ አሳውቋል።
ምንነታቸው ያልታወቁ ነገሮች መመልከቱን ጠፈርተኛው ተናግሯል።
ምንነታቸው ያልታወቀ ክስተቶች እንደተመለከቱ የተናገሩ ሰዎች ምስክርነት በሰነዶቹ ተካትቷል።
በ1957 ኤፍቢአይ ቃለ መጠይቅ ያደረገለት ግለሰብ ትልቅ፣ ክብ ተንቀሳቃሽ አካል ከምድር ሲነሳ መመልከቱን ገልጿል።
በ2023 በተደረገ ቃለ መጠይቅ ደግሞ ከደማቅ ብርሃን የሚወጣ ብረታማ ቁስ ሲንሳፈፍ ማየቱን አንድ አሜሪካዊ አስታውቋል።
ከ2022 አንስቶ በመካከለኛው ምሥራቅ የተሰማሩ የአሜሪካ ወታደሮች የሰጡት ምስክርነትም በሰነዶቹ ውስጥ ይገኛል።
ከኢራቅ፣ ከሶሪያ እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተገኙ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በፔንታገን ድረ ገጽ ላይ "ምንነታቸው ያልተለየ እንግዳ ክስተቶች" በሚል ተቀምጠዋል።
በ2022 የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምሥል በትክክል የት እንደሆነ ባልታወቀ የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ክብ ቅርጽ ያለው ቁስ ከግራ ወደ ቀኝ ሲንቀሳቀስ ያሳያል። "ምናልባት ሚሳዔል ሊሆን ይችላል" የሚል መግለጫ ከተንቀሳቃሽ ምሥሉ ጋር ተያይዞ ይነበባል።
የቴነሲ ሪፐብሊካን የምክር ቤት አባል ቲም ቡርቸት ዩፎዎችን በተመለከተ መንግሥት ከዚህም በላይ ግልጽ መሆን አለበት ብለዋል።
ፔንታገን የለቀቃቸው ሰነዶች "ጥሩ ጅማሮ ናቸው" ሲሉም በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
ትራምፕን በመደገፍ ይታወቁ የነበሩት እና አሁን ከፕሬዝዳንቱ ጋር የተጣሉት የቀድሞ የምክር ቤት አባል ማርጀሪ ቴይለር ግሪን በበኩላቸው እነዚህ ሰነዶች የተለቀቁት "አሜሪካውያን ከገጠሟቸው ችግሮች፣ ከሩሮ ውድነት እና ከኢራን ጦርነት ለማዘናጋት ነው" ብለው ተችተዋል።
"ይሄንን 'አንጸባራቂ ቁስ' እዩት የሚለው ፕሮፓጋንዳ በጣም ነው የሰለቸኝ" ሲሉም አጣጥለዋል።














