ሐማስ ትጥቅ ለመፍታት የቀረበለትን ዕቅድ ውድቅ አደረገ- የፍልስጤም ባለሥልጣን

ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ የሐማስ ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረሰው በጥቅምት ወር ቢሆንም እስካሁን ድረስ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገር አልቻለም
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሐማስ በትራምፕ የጋዛ የሰላም ጥረት ውስጥ የተቀመጠውን ትጥቅ የመፍታት ዕቅድ ውድቅ ማድረጉን ድርድሩን በቅርበት የሚከታተሉ የፍልስጤም ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።

በአሜሪካ የሚመራው የሰላም ቦርድ ውስጥ የጋዛ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ኒኮላይ ምላዴኖቭን ለእስራኤል አድልዎ አድርገዋል ሲልም ከስሷቸዋል።

ባለፈው ወር ምላዴኖቭ በጥቅምት ወር ሐማስ እና እስራኤል የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት ሁለተኛ ምዕራፍ ውስጥ ጋዛን ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ለማድረግ የሚያስችል ማዕቀፍ አቅርበዋል።

የፍልስጤም ባለሥልጣናት እንዳሉት ሐማስ ለቀጣናው አሸማጋዮች እስራኤል የመጀመሪያውን ምዕራፍ ስምምነቶችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እስክታደርግ ድረስ በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ውይይት እንደማያደርግ ነግሯቸዋል።

እስራኤል በበኩሏ የሐማስ ትጥቅ መፍታት ላይ ለውጥ ሳይታይ ምንም ዓይነት እርምጃ እንደማትወስድ ተናግራለች።

የሐማስ ልዑካን ቡድን ማክሰኞ ዕለት ካይሮን ለቅቀው ከመሄዳቸው በፊት የግብፅን የስለላ ኃላፊ እንዲያገኙ ታስቦ ነበር።

የትራምፕ የሰላም ዕቅድ የመጀመሪያ ምዕራፍ በጋዛ እየተካሄደ የነበረውን ጦርነት አስቁሟል።

ሐማስ አግቷቸው የነበሩ እስራኤላውያንን አንዲለቅ፤ በእስራኤል ወህኒ ቤት ውስጥ የነበሩ የፍልስጤም እስረኞችም እንዲለቀቁ ተደርጓል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጥር ወር አጋማሽ ላይ የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ትራምፕን ጦርነት ለማስቆም ያቀረቡት ዕቅድ ሁለተኛ ምዕራፍ መጀመሩን አስታውቀው ነበር።

ነገር ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ቆይቷል።

ሁለተኛው ምዕራፍ ጋዛን ከጦር እንቅስቃሴ ነጻ ማድረግ እና እስራኤል ሙሉ በሙሉ ጋዛን ለቅቃ እንድትወጣ በማድረግ በቋሚነት በአካባቢው የሚካሄደውን ጦርነትን ለማስቆም ያለመ ነው።

ባለፈው ወር ምላዴኖቭ በጋዛ የሚገኙ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች የጦር መሳሪያዎቻቸውን እንዲያስቀምጡ ዝርዝር ዕቅድ አውጥተው ነበር።

ይህም ግዛቱን ካወደመው የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ በኋላ ከሚደረገው የተሃድሶ ስራ መጀመር ጋር የተጣጣመ መሆኑን ያሳያል።

እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረቸው መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ እስራኤላውያን ላይ ጥቃት ከፍቶ 1200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው።

በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ከተኩስ አቁም በኋላ የተገደሉትን 757 ሰላማዊ ሰዎች ጨምሮ ከ72,330 በላይ መሞታቸውን የሐማስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

አንድ ከፍተኛ የሐማስ ባለሥልጣን ለቢቢሲ "ምላዴኖቭ እስራኤል የቀረውን የምዕራፍ አንድ ግዴታዎች እንድትወጣ የጊዜ ሰሌዳ ያቀርባሉ ብለን እየጠበቅን ነው፤ ከዚሁ ጋር የምዕራፍ ሁለት ውይይት ከመጀመሩ በፊት የእስራኤልን ጥሰቶች ለማስቆም ዋስትናዎችን እንዲያቀርብ እየጠበቅን ነው።"

የፍልስጤም አንጃዎች የጦር መሳሪያ ጉዳይን የፍልስጤም ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ከሚያረጋግጥ ሁሉን አቀፍ መፍትሄ ጋር የተቆራኘ አድርገው እንደሚመለከቱት አክለዋል።

ምላዴኖቭ እስራኤል ነፃ የሆነ የፍልስጤም መንግሥት መመስረትን እንደምትቀበል እምብዛም እንደማያምኑ ጨምረው ተናግረዋል።